[index]
amharique
አማርኛ
ስለሰብአዊ፡ መብቶች፡ ለማስተማር፡
የሚረዱ፡ አንዳን፡ ዘዴዎች።
በዩኔስኮ፡ ተዘጋጅቶ፡ በኢትዮጵያ፡ ብሄራዊ፡
ኮሚሽን፡ ተተረጎመ
አንቀጽ፡ ፩፤
የሰው፡ ልጅ፡ ሁሉ፡ ሲወለድ፡ ነጻና፡
በክብርና፡ በመብትም፡ እኩልነት፡ ያለው፡
ነው። ፡ የተፈጥሮ፡ ማስተዋልና፡ ሕሊና፡
ስላለው፡ አንዱ፡ ሌላውን፡ በወንድማማችነት፡
መንፈስ፡ መመልከት፡ ይገባዋል።
አንቀጽ፡ ፪፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የዘር፡ የቀለም፡ የጾታ፡
የቋንቋ፡ የሃይማኖት፡ የፖለቲካ፡ ወይም፡
የሌላ፡ ዓይነት፡ አስተሳሰብ፡ የብሔራዊ፡
ወይም፡ የኀብረተሰብ፡ ታሪክ፡ የሀብት፡
የትውልድ፡ ወይም፡ የሌላ፡ ደረጃ፡ ልዩነት፡
ሳይኖሩ፡ በዚሁ፡ ውሳኔ፡ የተዘረዘሩት፡
መብቶችንና፡ ነጻነቶች፡ ሁሉ፡ እንዲከበሩለት፡
ይገባል።
ከዚህም፡ በተቀረ፡ አንድ፡ ሰው፡ ከሚኖርበት፡
አገር፡ ወይም፡ ግዛት፡ የፖለቲካ፡ የአገዛዝ፡
ወይም፡ የኢንተርናሽናል፡ አቋም፡ የተነሳ፡
አገሩ፡ ነጻም፡ ሆነ፡ በሞግዚትነት፡ አስተዳደር፡
ወይም፡ እራሱን፡ ችሎ፡ የማይተዳደር፡
አገር፡ ተወላጅ፡ ቢሆንም፡ በማንኛውም፡
ዓይነት፡ ገደብ፡ ያለው፡ አገዛዝ፡ ሥር፡
ቢሆንም፡ ልዩነት፡ አይፈጸምበትም።
አንቀጽ፡ ፫፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የመኖር፣ ፡ በነጻነትና፡
በሰላም፡ የመኖሩ፡ መጠበቅ፡ መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፬፤
ማንም፡ ሰው፡ ቢሆን፡ በባርነት፡ አይገዛም።
፡ ባርነትና፡ የባሪያ፡ ንግድም፡ በማንኛውም፡
ዓይነት፡ ክልክል፡ ነው።
አንቀጽ፡ ፭፤
ማንም፡ ሰው፡ ቢሆን፡ የጭካኔ፡ ስቃይ፡
እንዳይደርስበት፡ ወይም፡ ከሰብዓዊ፡
አፈጻጸም፡ ውጭ፡ የሆነ፡ የተዋረድ፡ ተግባር፡
ወይም፡ ቅጣት፡ አይፈጸምበትም።
አንቀጽ፡ ፮፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በሕግ፡ ፊት፡ በሰው፡
ዘርነቱ፡ የመታወቅ፡ መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፯፤
ሰው፡ ሁሉ፡ በሕግ፡ ፊት፡ እኩል፡ ነው።
፡ ያለአንዳች፡ ልዩነትም፡ ሕጉ፡ ደህንነቱን፡
እንዲጠበቅለት፡ እኩል፡ የሆነ፡ መብት፡
አለው። ፡ ይህንን፡ ውሳኔ፡ በመጣስ፡ ከሚደረግ፡
ልዩነት፡ ለማድረግ፡ ከሚነሳሳ፡ እንዲጠበቅ፡
ሁሉም፡ የእኩል፡ መብት፡ አለው። ፡
አንቀጽ፡ ፰፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በሕገ፡ መንግስቱ፡
ወይም፡ በሕግ፡ የተሰጡትን፡ መሠረታዊ፡
መብቶች፡ ከሚጥሱ፡ ድርጊቶች፡ ከፍተኛ፡
በሆኑ፡ ብሔራዊ፡ የፍርድ፡ ባለስልጣኖች፡
ፍጹም፡ በሆነ፡ መንገድ፡ እንዲወገድለት፡
መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፱፤
ማንም፡ ሰው፡ ያለፍርድ፡ ተይዞ፡ እንዲታሰር፡
ወይም፡ በግዛት፡ እንዲኖር፡ አይደረግም።
አንቀጽ፡ ፲፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በመብቶቹና፡ በግዴታዎቹ፡
አፈጻጸም፡ እንዲሁም፡ በሚከሰስበት፡
ማንኛውም፡ ዓይነት፡ የወንጀል፡ ክስ፡
ነጻ፡ በሆነና፡ በማያዳላ፡ የፍርድ፡ ሸንጎ፡
በትክክለኛና፡ በይፋ፡ ጉዳዩ፡ እንዲሰማለት፡
የሙሉ፡ እኩልነት፡ መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፲፩፤
፩/፡ በወንጀል፡ ክስ፡ የተከሰሰ፡ ማንኛውም፡
ሰው፡ ለመከላከያው፡ አስፈላጊዎች፡ የሆኑትን፡
ሁሉ፡ አቅርቦ፡ በሚከራከርበት፡ የይፋ፡
ፍርድ፡ ቤት፡ በሕግ፡ መሠረት፡ ወንጀለኛ፡
መሆኑ፡ እስቲረጋገጥበት፡ ድረስ፡ ከወንጀል፡
ነጻ፡ እንደሆነ፡ የመቆጠር፡ መብት፡ አለው።
፪/፡ ማንም፡ ሰው፡ በብሔራዊ፡ ወይም፡ በኢንተርናሽናል፡
ሕግ፡ አንድ፡ ነገር፡ ወንጀል፡ ሆኖ፡ ባልተደነገገበት፡
ጊዜ፡ በፈጸመው፡ ወይም፡ ባልፈጸመው፡
ማንኛውም፡ ሥራ፡ ወንጀለኛ፡ ሆኖ፡ አይከሰስም።
፡ ወይም፡ ወንጀሉ፡ በተፈጸመበት፡ ጊዜ፡
ከተደነገገው፡ ቅጣት፡ ይበልጥ፡ አይፈረድበትም።
አንቀጽ፡ ፲፪፤
ማንም፡ ሰው፡ በግል፡ ኑሮው፡ በቤተሰቡ፡
ውስጥ፡ በቤቱ፡ ወይም፡ በሚጻጻፈው፡ ደብዳቤ፡
በፍርድ፡ ያልተለየ፡ ጣልቃ፡ ገብነት፡
ወይም፡ ክብሩን፡ የሚነካና፡ ስሙን፡ የሚያጎድፍ፡
ተቃውሞ፡ አይፈጸምበትም። ፡ እያንዳንዱ፡
ሰው፡ ከእንደዚህ፡ ያለ፡ ጣልቃ፡ ገብነት፡
ወይም፡ የሚጎዳ፡ ተግባር፡ ሕግ፡ እንዲከላከልለት፡
መብት፡ አለው። ፡
አንቀጽ፡ ፲፫፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በየብሔራዊ፡ ወሰን፡
ክልሉ፡ የመዘዋወርና፡ የመኖር፡ ነጻነት፡
መብት፡ አለው።
፪/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ ከማንኛውም፡ አገር፡
ሆነ፡ ከራሱ፡ አገር፡ ወጥቶ፡ እንደገና፡
ወደ፡ አገሩ፡ የመመለስ፡ መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፲፬፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ ከጭቆና፡ ሸሽቶ፡
በሌሎች፡ አገሮች፡ ጥገኝነትን፡ የመጠየቅና፡
በደህና፡ የመኖር፡ መብት፡ አለው።
፪/፡ ፖለቲካዊ፡ ካልሆኑ፡ ወንጀሎች፡ ወይም፡
የተባበሩት፡ መንግሥታት፡ ድርጅት፡ ዋና፡
ዓላማዎችን፡ ከሚቃረኑ፡ ሥራዎች፡ የተነሳ፡
በሚደርሱ፡ ክሶች፡ ምክንያት፡ ከሆነ፡
ይህ፡ መብት፡ ሊያገለግል፡ አይችልም።
አንቀጽ፡ ፲፭፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የዜግነት፡ መብት፡
አለው።
፪/፡ ማንም፡ ሰው፡ ያለፍርድ፡ ዜግነቱ፡
አይወሰድበትም፡ ወይም፡ ዜግነቱን፡ የመለወጥ፡
መብት፡ አይነፈገውም።
አንቀጽ፡ ፲፮፤
፩/፡ አካለ፡ መጠን፡ የደረሱ፡ ወንዶችና፡
ሴቶች፡ በዘር፡ በዜግነት፡ ወይም፡ በሃይማኖት፡
ልዩነት፡ ሳይወሰኑ፡ ጋብቻን፡ የመፈጸምና፡
ቤተሰብን፡ የመመሥረት፡ መብት፡ አላቸው፤
፡ ጋብቻ፡ በመፈጸም፡ በጋብቻ፡ ጊዜና፡
ጋብቻ፡ በሚፈርስበትም፡ ጊዜ፡ እኩል፡
መብት፡ አላቸው።
፪/፡ ጋብቻ፡ የሚፈጸመው፡ ጋብቻ፡ ለመፈጸም፡
በሚፈልጉ፡ ሁለቱም፡ ወገኖች፡ በሚያደርጉት፡
ነጻና፡ ሙሉ፡ ስምምነት፡ መሠረት፡ ብቻ፡
ነው።
፫/፡ ቤተሰብ፡ በኀብረ፡ ሰብ፡ የተፈጥሮና፡
መሰረታዊ፡ ክፍል፡ ስለሆነ፡ በኀብረሰቡና፡
በመንግሥቱም፡ ደህንነቱ፡ እንዲጠበቅለት፡
ይገባል።
አንቀጽ፡ ፲፯፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ ብቻውን፡ ወይም፡
ከሌሎች፡ ጋር፡ በኀብረት፡ ሆኖ፡ የኀብረት፡
ባለቤትነት፡ መብት፡ አለው።
፪/፡ ማንም፡ ሰው፡ ያለፍርድ፡ ንብረቱ፡
አይወሰድበትም።
አንቀጽ፡ ፲፰፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የሃሳብ፡ የሕሊናና፡
የሃይማኖት፡ ነጻነት፡ መብት፡ አለው።
፡ ይህም፡ መብት፡ ሃይማኖቱን፡ ወይም፡
እምነቱን፡ የመለወጥ፡ ነጻነትንና፡ ብቻውን፡
ወይም፡ ከሌሎች፡ ጋር፡ በኀብረት፡ በይፋ፡
ወይም፡ በግል፡ ሆኖ፡ ሃይማኖቱን፡ ወይም፡
እምነቱን፡ የማስተማር፣ ፡ በተግባር፡
የመግለጽ፡ የማምለክና፡ የማክበር፡ ነጻነትን፡
ይጨምራል።
አንቀጽ፡ ፲፱፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የሐሳብና፡ ሐሳቡን፡
የመግለጽ፡ መብት፡ አለው። ፡ ይህም፡ መብት፡
ያለጣልቃ፡ ገብነት፡ በሐሳብ፡ የመጽናትንና፡
ዜናን፡ ወይም፡ ሐሳቦችን፡ ያላንዳች፡
የድንበር፡ ገደብ፡ የማግኘትን፡ የመቀበልንና፡
ወይም፡ የማካፈልን፡ ነጻነትም፡ ይጨምራል።
አንቀጽ፡ ፳፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በሰላም፡ የመሰብሰብና፡
ግንኙነት፡ የማድረግ፡ ነጻነት፡ መብት፡
አለው።
፪/፡ ማንም፡ ሰው፡ የአንድ፡ ማኀበር፡ አባል፡
እንዲሆን፡ አይገደድም።
አንቀጽ፡ ፳፩፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በቀጥታ፡ ወይም፡
ነጻ፡ በሆነ፡ መንገድ፡ በተመረጡ፡ እንደራሴዎች፡
አማካኝነት፡ በአገሩ፡ መንግስት፡ የመካፈል፡
መብት፡ አለው።
፪/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በአገሩ፡ የህዝብ፡
አገልግሎት፡ እኩል፡ የማግኘት፡ መብት፡
አለው።
፫/፡ የመንግስት፡ ሥልጣን፡ መሠረቱ፡ የሕዝቡ፡
ፈቃድ፡ መሆን፡ አለበት። ፡ ይህም፡ ፈቃድ፡
ለሁሉም፡ እኩል፡ በሆነ፡ በምሥጢር፡ በሚደረግ፡
የድምፅ፡ መስጠት፡ ምርጫ፡ ወይም፡ በተመሳሳይ፡
ሁኔታ፡ በየጊዜውና፡ በትክክል፡ በሚፈጸሙ፡
ምርጫዎች፡ እንዲገለጽ፡ መሆን፡ አለበት።
አንቀጽ፡ ፳፪፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የኀብረ፡ ሰብ፡ አባል፡
እንደመሆኑ፡ በኀብረ፡ ሰብ፡ ደህንነቱ፡
እንዲጠበቅ፡ መብት፡ አለው። ፡ እንዲሁም፡
በብሔራዊ፡ ጥረትና፡ በኢንተርናሽናል፡
መተባበር፡ አማካይነትና፡ በእያንዳንዱ፡
መንግስት፡ ድርጅትም፡ የሀብት፡ ምንጮች፡
መሰረት፡ ለክብሩና፡ ለሰብዓዊ፡ አቅሙ፡
ነጻ፡ እድገት፡ የግድ፡ አስፈላጊ፡ የሆኑት፡
የኤኮኖሚ፡ የማኀበራዊ፡ ኑሮና፡ የባህል፡
መብቶች፡ በተግባር፡ እንዲገለጹለት፡
መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፳፫፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የመሥራት፡ የሥራ፡
ነጻ፡ ምርጫና፡ ለሥራም፡ ትክክለኛና፡
ተስማሚ፡ የአሠራር፡ ሁኔታዎችና፡ ሥራም፡
እንዳያጣ፡ መብት፡ አለው።
፪/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ ያላንዳች፡ ልዩነት፡
ማድረግ፡ ለአንድ፡ ዓይነት፡ ሥራ፡ እኩል፡
የሆነ፡ ደመወዝ፡ የማግኘት፡ መብት፡ አለው።
፫/፡ በሥራ፡ ላይ፡ ያለ፡ ሰው፡ ለእራሱና፡
ለቤተሰቡ፡ ለሰብዓዊ፡ ክብር፡ ተገቢ፡
የሆነ፡ ኑሮን፡ የሚያስገኝለትና፡ ካስፈለገም፡
በሌሎች፡ የኀብረሰብ፡ ደህንነት፡ መጠበቂያ፡
ዘዴዎች፡ የተደገፈ፡ ትክክለኛና፡ ተስማሚ፡
ዋጋውን፡ የማግኘት፡ መብት፡ አለው።
፬/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ ጥቅሞቹን፡ ለማስከበር፡
የሙያ፡ ማኀበሮችን፡ ለማቋቋምና፡ ማኀበርተኛ፡
ለመሆን፡ መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፳፬፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የዕረፍትና፡ የመዝናናት፡
እንዲሁም፡ በአግባብ፡ የተወሰኑ፡ የሥራ፡
ሰዓቶች፡ እንዲኖሩትና፡ በየጊዜው፡ የዕረፍት፡
ጊዜያትን፡ ከደመወዝ፡ ጋር፡ የማግኘት፡
መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፳፭፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ ለእራሱና፡ ለቤተሰቡ፡
ጤንነትና፡ ደህንነት፡ ምግብ፣ ፡ ልብስ፣
፡ ቤትና፡ ሕክምና፡ አስፈላጊ፡ የማኀበራዊ፡
ኑሮ፡ አገልግሎቶችም፡ ጭምር፡ የሚበቃ፡
የኑሮ፡ ደረጃ፡ ለማግኘት፡ መብት፡ አለው።
፡ ሥራ፡ ሳይቀጠር፡ ቢቀር፡ ቢታመም፡ ለመሥራት፡
ባይችል፡ ባል፡ ወይም፡ ሚስት፡ ቢሞት፡
ቢያረጅ፡ ወይም፡ ከቁጥጥሩ፡ ውጭ፡ በሆኑ፡
ምክንያቶች፡ መሰናከል፡ ቢገጥመው፡ ደህንነቱ፡
እንዲጠበቅለት፡ መብት፡ አለው።
፪/፡ ወላድነትና፡ ሕጻንነት፡ ልዩ፡ ጥንቃቄና፡
እርዳታ፡ የማግኘት፡ መብት፡ አላቸው፤
፡ በጋብቻ፡ ወይም፡ ያለጋብቻ፡ የሚወለዱ፡
ሕጻናትም፡ የተመሳሳይ፡ የደህንነታቸው፡
መጠበቅ፡ መብት፡ አላቸው።
አንቀጽ፡ ፳፮፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የመማር፡ መብት፡
አለው። ፡ ትምህርት፡ ቢያንስ፡ ቢያንስ፡
በአንደኛ፡ ደረጃና፡ በመሰረታዊ፡ ደረጃዎች፡
በነጻ፡ ሊሆን፡ ይገባል። ፡ የአንደኛ፡
ደረጃ፡ ትምህርት፡ መማር፡ ግዴታ፡ ነው።
፡ የቴክኒክና፡ የልዩ፡ ልዩ፡ ሙያ፡ ትምህርት፡
በጠቅላላው፡ የከፍተኛ፡ ደረጃ፡ ደግሞ፡
በችሎታ፡ መሠረት፡ ለሁሉም፡ እኩል፡ መሰጠት፡
አለበት።
፪/፡ ትምህርት፡ ለእያንዳንዱ፡ ሰው፡ ሁኔታ፡
ማሻሻያና፡ ለሰብዓዊ፡ መብቶችም፡ መሠረታዊ፡
ነጻነቶች፡ ክብር፡ ማዳበርያ፡ የሚውል፡
መሆን፡ አለበት። ፡ እንዲሁም፡ የተለያየ፡
ዘር፡ ወይም፡ ሃይማኖት፡ ባሏቸው፡ ሕዝቦች፡
መካከል፡ ሁሉ፡ መግባባትን፡ ተቻችሎ፡
የመኖርንና፡ የመተባበርን፡ መንፈስ፡
የሚያጠነክርና፡ የተባበሩት፡ መንግሥታት፡
ድርጅት፡ ሰላምን፡ ለመጠበቅ፡ የሚፈጽማቸው፡
ተግባሮች፡ እንዲስፋፋ፡ የሚያበረታቱ፡
መሆን፡ አለበት። ፡
፫/፡ ወላጆች፡ ለልጆቻቸው፡ ለመስጠት፡
የሚፈልጉትን፡ ትምህርት፡ ለመምረጥ፡
የቅድሚያ፡ መብት፡ አላችው። ፡
አንቀጽ፡ ፳፯፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በኀብረ፡ ሰቡ፡
የባህል፡ ኑሮ፡ በነጻ፡ መካፈልና፡ በኪነ፡
ጥበብ፡ ለመጠቀም፡ በሳይንስ፡ እርምጃና፡
በጥቅሞቹም፡ ለመሳተፍ፡ መብት፡ አለው።
፡
፪/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ ከደረሰው፡ ማንኛውም፡
የሳይንስ፡ የድርሰትና፡ የኪነ፡ ጥበብ፡
ሥራ፡ የሚያገኘው፡ የሞራሉንና፡ የሃብት፡
ጥቅሞች፡ እንዲከበሩለት፡ መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፳፰፤
እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በዚህ፡ ውሳን፡ ውስጥ፡
የተዘረዘሩት፡ መብቶችና፡ ነጻነቶች፡
በሙሉ፡ በተግባር፡ እንዲውሉ፡ ለሚደረግባቸው፡
የኀብረሰብና፡ የኢንተርናሽናል፡ ሥርዓት፡
የመጠቀም፡ መብት፡ አለው።
አንቀጽ፡ ፳፱፤
፩/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ የራሱ፡ ነጻነትና፡
ሙሉ፡ መሻሻል፡ በሚያገኝበት፡ ኀብረሰብ፡
ውስጥ፡ የሚፈጽማቸው፡ ግዴታዎች፡ ይኖሩበታል።
፪/፡ እያንዳንዱ፡ ሰው፡ በመብቶቹ፡ በነጻነቶቹ፡
በሚጠቀምበት፡ ጊዜ፡ የሚታገደው፡ የሌሎችን፡
መብቶችና፡ ነጻነቶች፡ በሚገባ፡ ለማሰከበር፡
ብቻ፡ በተደነገጉ፡ ሕጎችና፡ የግብረ፡
ገብነትን፡ የጠቅላላውን፡ ሕዝብ፡ ፀጥታና፡
ደህንነት፡ በዴሞክራቲክ፡ ማኀበራዊ፡
ኑሮ፡ ትክክለኛ፡ የሆነው፡ ተፈላጊ፡ ጉዳይ፡
ለማርካት፡ በተወሰነው፡ ብቻ፡ ነው።
፫/፡ እነዚህ፡ መብቶችና፡ ነፃነቶች፡ በማንኛውም፡
ሁኔታ፡ የተባበሩት፡ መንግሥታት፡ ድርጅት፡
መሰረት፡ ዓላማዎች፡ ተቃራኒ፡ በሆነ፡
መንገድ፡ ሊፈጸሙ፡ አይገባቸውም።
አንቀጽ፡ ፴፤
በዚህ፡ ውሳኔ፡ ከላይ፡ የተዘረዘረው፡
ሁሉ፡ በዚሁ፡ ውስጥ፡ የተጠቀሱትን፡ ማናቸውም፡
መብቶች፡ ወይም፡ ነጻነቶች፡ ለማበላሸት፡
በታሰበ፡ ማንኛውም፡ ዓይነት፡ ተግባር፡
ለማዋል፡ ወይም፡ ድርጊትን፡ ለመፈጸም፡
ለማንኛውም፡ መንግሥት፡ ወይም፡ ድርጅት፡
ወይም፡ ሰው፡ የተባሉ፡ አይተረጎሙም።
[index]